
²³እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ ²⁴እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ²⁵ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ²⁶ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ ²⁷እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። ²⁸ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።
ዕብ. 7፥23–28
መግቢያ በዚህ ክፍል እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ለማዳን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመሠረተውን አዲሱን ኪዳን እንመለከታለን። በዚህም ኪዳን የሚያገለግለውን ታላቁንና ዘላለማዊ የሆነውን ሊቀ-ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመለከታለን።
በመጀመሪያ እንደምናውቀው በኃጢአት የወደቀው የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል እግዚአብሔር አምላክ እራሱ ወደ አዳም መጣ። ይህንንም ያደረገው ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ነበር። ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ ሕጉን ሲሰጥ ለኃጢአት ማስተሰርያ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን የተለያዩ የእንስሳት የመሥዋዕት ሥርዓትን አብሮ ሰጥቶ ነበር። በዚህም በቀደመው ኪዳን ካህናቱ በየጊዜውና በዕየለቱ የተለያዩ መሥዋዕቶችን በማቅረብ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ሊቀ-ካህኑ ለእራሱና ለሕዝቡ የሚሆን የኃጢአት ስርየት መሥዋዕትን በማቅረብ በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ውስንነት በነበረው በቀደመው ኪዳን ያገለግሉ ነበር ዘሌ. 9፥8–15። ይህ ሁሉ ግን የሕዝቡንም ሆነ የካህናቱን ሕሊና ሊያነፃና ሊያድን የማይችል የሥጋ ስርዓት ብቻ ነበር።
በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ ይህን የቀደመውን ኪዳን ሽሮ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ የመሥዋዕት በግ እንዲሆን ፈቅዶ፣ መጥቶም ፍጹም አምላክና ሰው ሆኖ ሞቶ አዲሱን ኪዳን ከፈተ። ይህ አዲሱ ኪዳን እግዚአብሔር በቀጠረው ጊዜ ሆኖአል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ማስታረቅ ችሏል። በዚህም ክፍል እንደምናየው ይህ አዲሱ ኪዳን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነልን ፡-
- ስለ እኛ ሊማልድ ዘወትር የሚኖር (ቁ. 25)
- ለዘላለም የሚኖር እና የማይለወጥ ክህነት ያለው ሊቀ-ካህን (ቁ. 24)
- በእርሱ በኩል የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድን የሚችል (ቁ. 25)
- ፍጹም የሆነ የመሥዋዕት በግ፣ ቅዱስና ተንኮል የሌለበት (ቁ. 26)
- ዕለት ዕለት መሥዋዕት ማቅረብ የማያስፈልገው፣ አንድ ጊዜ የፈጸመ (ቁ. 27) መሆኑን ማየት እንችላለን፡፡
በዚህ አዲሱ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ በኩል የመጣነውን ፈጽሞ ካዳነን በኋላ ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ደግሞ አለው፡፡ እርሱም፡- ለሌሎች ይህንን ታላቅ የማዳን ሥራ በማስታወቅ እነርሱ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ማድረግ ነው፡፡
የጽሑፍ ዝግጅት፡ ብሌን ሙሉጌታ